2 Corinthians 4

በሸክላ ውስጥ የተቀመጠ ክቡር ዕቃ

1ስለዚህ ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ይህ አገልግሎት ስላለን ተስፋ አንቈርጥም። 2ነገር ግን ስውርና አሳፋሪ ነገሮችን ትተናል፤ አናታልልም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ከሐሰት ጋር አንቀላቅልም፤ ይልቁንም እውነትን በግልጽ እየተናገርን በሰው ሁሉ ኅሊና ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረን ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት እናቀርባለን።

3ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ፣ የተከደነው ለሚጠፉት ነው። 4የእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን የክርስቶስ፣ የክብሩን ወንጌል ብርሃን እንዳያዩ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን ሰዎች ልቡና አሳውሯል። 5እኛ የምንሰብከው ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታ መሆኑን እንጂ ራሳችንን አይደለምና፤ እኛም ራሳችን ስለ ኢየሱስ ስንል የእናንተ አገልጋዮች ሆነናል። 6በክርስቶስ ፊት እግዚአብሔር የክብሩን ዕውቀት ብርሃን ይሰጠን ዘንድ፣ “በጨለማ ብርሃን ይብራ” ያለው እግዚአብሔር ብርሃኑን በልባችን አብርቷልና።

7ነገር ግን ይህ እጅግ ታላቅ ኀይል ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ አለመሆኑን ለማሳየት፣ ይህ የከበረ ነገር በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን። 8ከየአቅጣጫው ብንገፋም አንንኰታኰትም፤ ግራ ብንጋባም ተስፋ አንቈርጥም፤ 9ብንሰደድም ተጥለን አንቀርም፤ መትተው ቢጥሉንም አንጠፋም። 10የኢየሱስ ሕይወት በሰውነታችን እንዲገለጥ፣ የኢየሱስን ሞት ዘወትር በሰውነታችን ተሸክመን እንዞራለን። 11የኢየሱስ ሕይወት ሟች በሆነው ሥጋችን እንዲገለጥ፣ እኛ ሕያዋን የሆንን ሁልጊዜ ስለ ኢየሱስ ለሞት ዐልፈን እንሰጣለንና። 12እንግዲህ ሞት በእኛ ይሠራል፤ ሕይወት ግን በእናንተ።

13“አመንሁ፤ ስለዚህም ተናገርሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ እኛም በዚያው የእምነት መንፈስ እናምናለን፤ ስለዚህም እንናገራለን፤ 14ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እኛንም ደግሞ ከኢየሱስ ጋር አስነሥቶ ከእናንተ ጋር በፊቱ እንደሚያቀርበን እናውቃለን። 15ለብዙ ሰዎች እየደረሰ ያለው ጸጋ፣ ለእግዚአብሔር ክብር በምስጋና ላይ ምስጋናን እንዲጨምር ይህ ሁሉ ለእናንተ ጥቅም ሆኗል።

16ስለዚህ ተስፋ አንቈርጥም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ፣ ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤ 17ምክንያቱም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል። 18ስለዚህ ዐይናችን የሚያተኵረው በሚታየው ነገር ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ነው፤ የሚታየው ጊዜያዊ ነውና፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው።

Copyright information for AmhNASV